የወላይታ ዞን አስተዳደር በዞኑ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች የተለያዩ የሚዲያ መረጃዎችን በማግኘት ከድህነትና ኋላቀርነት እንዲወጣ እና የህዝቡ ተጠቃሚነት ወደ ላቀ ደረጃ እንዲደርስ ለማድረግ የሚያስችል የረዥምና የመካከለኛ ዘመን እቅድ በማዘጋጀት ፈጣንና ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ ዕድገት ለማስመዝገብ በተደረገው ጥረት ባለፉት ዓመታት በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ መስኮች የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ተችሏል፡፡
ባለፉት ዓመታት በልማት፣ በሰላም፣ በመልካም አስተዳደርና በዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ሂደቶች የተመዘገቡ ውጤቶችን በማስቀጠል በሚቀጥሉት ዓመታት የዞኑን ህዝብ የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችል ከ2013 እስከ 2017 ዓ.ም ድረስ የሚዘልቅ የአምስት ዓመታት ስትራቴጂክ እቅድ አዘጋጅቶ ወደ ትግበራ ውስጥ ገብቷል፡፡ በዚህም ስትራቴጂክ እቅድ ውስጥ ከተካተቱት ዋና ዋና ጉዳዮች መካከል የወላይታ ቴሌቪዥን በማቋቋም ዞናዊ፣ ክልላዊና ሀገር አቀፋዊ መረጃዎችን ለዞኑ ህዝብ በቋንቋው ተደራሽ ማድረግ አንዱ ነው፡፡ ለእቅዱ ተግባራዊነት የዞኑ አስተዳደርና ምልዓተ ህዝቡ እጅ ለእጅ ተያይዘው በተነሳሽነትና በባለቤትነት መንፈስ እንዲረባረቡበት ማድረግ ከተቻለ አገራችን መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ ለመሰለፍ የሚታደርገውን ጥረት ማሳካት እንደሚቻል ያለፉት ዓመታት የእቅድ አፈጻጸም ተሞክሮዎች ያመለክታሉ፡፡
ለወላይታ ህዝብ ወቅታዊ መረጃዎችን ማሰራጨት የሚችል ቴሌቪዥን በማቋቋም፣ በዞኑ የተለያዩ ወቅታዊ መረጃዎችን ለህብረተሰቡ ማድረስ የሚችሉ ብቃትና የተሟላ ክህሎት ያላቸው ጋዜጠኞችና ኮሚኒኬተሮችን በማፍራትና ወጥነት ያለው የመረጃ ፍሰት እንዲኖር በማስቻል ህብረተሰቡ በሀገራዊና ክልላዊ ጉዳዮች ዙሪያ ብሔራዊ መግባባት እንዲፈጥር ለማስቻል በስትራቴጂክ ዕቅዱ ውስጥ ግብ ተቀምጧል፡፡
በተቀመጠው ግብ መሠረት የዞኑ አስተዳደር ህብረተሰቡን በማስተባበርና በማሳተፍ የወላይታ ቴሌቪዥን ጣቢያ እንዲቋቋምና ጣቢያው የተጣለበትን የማሳወቅ፣ የማስተማር፣ የማዝናናትና ህዝቡን ለልማት የማነሳሳት ዓላማዎችን በብቃት እንዲወጣ ለማስቻል ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ይገኛል፡፡ ቴሌቪዥኑ የዞኑን፣ የክልሉን ብሎም የሀገራችን ኢኮኖሚያዊ ማህበራዊና ፖለቲካዊ እድገት ወደ ላቀ ደረጃ እንዲሸጋገር በሚደረገው ጥረት የሚጠቅበትን የራሱን ድርሻ በብቃት እንዲወጣ ለማስቻል ታስቦ የተቋቋመ ተቋም እንደመሆኑ መጠን የተጣለበትን ተልዕኮ ከግብ እንዲያደርስ የሁሉም የተቀናጀ ትኩረት ያስፈልጋል።
የወላይታ ቴሌቪዥን እንዲቋቋም የተፈለገበት ዋና ዓላማም የወላይታ ዞን ባለፉት ዓመታት የዞኑን ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ እድገት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር የቴሌቪዥን ሚዲያ በአካባቢው ባለመኖሩ ለተለያዩ የሚዲያ ተቋማት ከፍተኛ የሆነ መዋዕለ ንዋይ በመክፈል የዞኑን ህዝብ ባህላዊና ታሪካዊ መረጃዎችን ተደራሽ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡
የዞኑ አስተዳደር የህዝቡን የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ከዚህ ቀደም ለተለያዩ የሚዲያ ተቋማት ከፍተኛ የሆነ መዋዕለ ንዋይ በመክፈል የሚያሰራጨውን የአየር ሰዓት ኪራይ ከማስቀረት ባለፈ ለወላይታ ህዝብ በቋንቋው መረጃዎችን ተደራሽ የሚያሰራጭ የ24 ሰዓት የቴሌቪዥን ስርጭት በመጀመር ህዝቡ በራሱ ቻናል የ24 ሰዓት የቴሌቪዥን ስርጭት እንዲያገኝ ተደርጓል፡፡
ሚዲያው የመንግስት ፖሊሲዎች፣ ስትራቴጂዎችና ፕሮግራሞች ላይ አትኩሮ እንዲሠራ ለማስቻል በክልሉ ውስጥ የሚገኙ አቻ ሚዲያዎች በተጨማሪ በፌዴራል ደረጃ የሚገኙ ትላልቅ ሚዲያዎች እና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ለጋዜጠኞችና ለቴክኖሎጂ ባለሙያዎች በፖሊሲና ስትራቴጂዎች እንዲሁም በፕሮፌሺናል ጋዜጠኝነት ሙያ ዙሪያ ስልጠናዎችን እንዲሰጡ በማድረግ የዳበረ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ተደርጓል፡፡
የወላይታ ቴሌቪዥን አዲስ የተቋቋመ ተቋም ከመሆኑ ጋር ተያይዞ አሁን እየተስተዋለ ያለውን የተሽከርካሪ እጥረት ለመቅረፍ የዞኑ አስተዳደር እያደረገ ያለው ጥረት ሊበረታታ የሚገባ ጉዳይ ቢሆንም ሚዲያው የ24 ሰዓት ስርጭት የሚያካሂድ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ብዙ ትኩረትና ድጋፍ የሚያስፈልገው ነው፡፡
ከዚህም ባሻገር ሚዲያው ከሌሎች አቻ ሚዲያዎች ጋር ተወዳዳሪ እንዲሆን በጥናት የተደገፈ የጥራት ማረጋገጫ ስራ ሊሠራ የሚገባው መሆኑ እና የሚዲያው የማስፈጸም አቅም ግንባታ ጋር ተያይዞ የአመራርና የፈፃሚዎችን አቅም በቀጣይነት ማሳደግ የሚያስፈልግ መሆኑ አያጠራጥርም፡፡
የወላይታ ቴሌቪዥን በበቂ የሰው ኃይልና ማቴሪያል እንዲደራጅ ማድረግ ትልቅ ትኩረት የሚያስፈልገው ሲሆን የተቋሙ የሰው ኃይል መዋቅር በአማካሪ ድርጅቶች በተደራጀ ሁኔታ ማስጠናት ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ ነው፡፡
የወላይታ ቴሌቪዥን ጣቢያ አሁን ያለበት ህንፃ ለሚዲያ ሥራ አመቺ በሆነ መንገድ ሳይሆን ለሌላ ዓላማ የተገነባ በመሆኑ ዋናው የቴሌቪዥን ጣቢያ ስቱዲዮና ቢሮ ግንባታ ለማከናወን በቀጣይ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ከመሆኑ ባለፈ በጣቢያው ጎልቶ የሚታየውን የመብራት ችግር በዘላቂነት ለመቅረፍ ለቴሌቪዥን ጣቢያው ብቻ አገልግሎት የሚሰጥ ትራንስፎርሜር የሚያስፈልገው መሆኑ ሊታወቅ ይገባል፡፡ ከዚህም ባሻገር የመብራት መቆራረጥ በሚታይበት ወቅት ተክቶ ሊሠራ የሚችል ሁል ጊዜ ዝግጁ የሆነ ጄነሬተር እንደሚያስፈልገው ታውቆ ትኩረት ተሰጥቷል፡፡
የወላይታ ቴሌቪዥን ሕብረተሰቡን እያዝናና በማስተማር፣ ወቅታዊና ትክክለኛ መረጃዎችን ከመንግሥት ለሕዝብ፣ ከሕዝብም ለመንግሥት በማድረስ፤ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓቶችን በማስገንዘብ፣ የሕዝብ መብትና ግዴታዎችን በማሳወቅና ተግባራዊ እንዲደረጉም በማስተማሩ ሂደትና ሕዝቦች ተከባብረው በጋራና በሠላም በመኖር ለጋራ ሀገራዊ ልማት ተሳታፊ እንዲሆኑ በማስቻል ረገድ የተጣለበትን ኃላፊነት በብቃት እንዲወጣ የተቋቋመው የወላይታ ቴሌቪዥን የደቡብ ክልል ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት እና የሲዳማ ሚዲያ ኔትወርክ አደረጃጀትን ቤንች ማርክ በማድረግ ተጠንቶ ከኢፌዴሪ ብሮድካስት ባለስልጣን በተሰጠው ፈቃድ መሠረት የሰው ሃይል በምደባ፣ በዝውውርና በቅጥር በማሟላት የሙከራ ስርጭትን በየካቲት 2/2013 ዓ.ም ጀምሯል፡፡
አንድ ህዝብ ቋንቋውን፣ ባህሉን ታሪኩንና ሌሎች ትውፊቶቹን ጠብቆ እንዲያኖር እና እንዲያሳድግ ለማድረግ ከሚያስፈልጉት ዋና ዋና መሳሪያዎች አንዱ ሚዲያ ነው፡፡ በመሆኑም የወላይታ ቴሌቪዥን ጽ/ቤት ዞኑ አስተዳደርና ህዝብ የተጣለበትን ሃላፊነት በብቃት መወጣት ይችል ዘንድ የብሮድካስት አዋጆችና መመሪያዎችን እንዲሁም የተቋሙን ኤዲቶሪያል ፖሊሲ መሠረት በማድረግ ለዞኑ ህዝብ ወቅታዊና ትክክለኛ መረጃ ተደራሽ ለማድረግ ተቋቁሞ በትኩረት እየሠራ ይገኛል፡፡
የመንግሥትንም ፖሊሲና ስትራቴጂ ወደ ሕዝቡ ከማስረጽና ህዝቡንም ለተሳታፊነት ከማነሳሳት አንፃር ሚዲያ ወሳኝ በመሆኑ በዞኑ ጎጂ ልማዶችን እንዲወገዱና የተሻሻሉ የአመራረት ዘይቤዎችን በመከተል ህብረተሰቡን ወደ ዘመናዊ የአኗኗር ሥርዓት ለማምጣት ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡
የዞኑ ሕዝብ የመረጃ ፍላጎቱ እንዲሟላና የበለጠ የሚዲያ ተጠቃሚ እንዲሆን የቴሌቪዥን ጽ/ቤቱ በቀን ለ24 ሰአት ወቅታዊ ዜናዎች፣ የተለያዩ ትምህርታዊ እና መዝናኛ ፕሮግራሞችን ለማሰራጨት ግብ ጥሎ የተለያዩ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን በማከናወን ላይ ሲሆን በቀጣይም ከተባባሪ አካላት ጋር ስምምነቶችን በመፍጠር አዝናኝ እና አስተማሪ ፕሮግራሞችን በማቅረብ ሚዲያውን ተመራጭ ለማድረግ የሁሉም ባለ ድርሻ አካላት ትብብር ያስፈልጋል፡፡
የወላይታ ቴሌቪዥን የአገሪቱን እና የክልሉን ራዕይ መሰረት በማድረግ ከኢፌዴሪ ብሮድካስት ባለስልጣን እና ከዞኑ አስተዳደርና ህዝብ የተሰጡትን ተልእኮዎች ለመፈጸም የያዛቸው ራእይ፣ ተልእኮ እና ዕሴቶች እንዲሁም የወላይታ ቴሌቪዥን ጣቢያ የተቋቋመለት አላማ ከዚህ በታች እንደሚከተለ ቀርበዋል፡፡
የተጀመረውን ሀገራዊ ለውጥ፣ የልማት፣ የመልካም አስተዳደርና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ የሚያፋጥኑ መረጃዎችን በብቃትና በጥራት በማሠራጨት በሚቀጥሉት 15 ዓመታት በዞኑ በመረጃ የበለፀገ ማህበረሰብ ተፈጥሮ ማየት፡፡
ሕገ-መንግሥታዊና ዴሞክራሲያዊ መርሆዎችን የጠበቁና ማህበረሰቡን ያሳተፉ ወቅታዊ፣ ሚዛናዊ፣ አስተማሪና አዝናኝ መረጃዎችን እንዲሁም ፕሮግራሞችን በማህበረሰቡ እና በሌሎች ቋንቋዎች በማስተላለፍ የዞኑን ማህበረሰብ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ሕይወት ንቃተ-ህሊና ዳብሮ ወደ ተሻለ ደረጃ እንዲደርስ ማገዝ፡፡
እያዝናኑ ማስተማር
ሙያዊ ሥነ-ምግባር
ወቅታዊነትና ተአማኒነት ያለዉ መረጃ
ሚዛናዊነትና ተጨባጭነት
ሐቀኝነትና ተሳትፎአዊነት
ግልጸኝነትና ተጠያቂነት
ተከታታይነት ያለው መሻሻል
ከሙስና የፀዳ አሠራር
በዞኑ፣ በክልሉና በፌዴራሉ ህገ-መንግስት የተቀረጹ ፖሊሲዎች፣ ህጎች፣ ደንቦችና መመሪያዎች መሰረት ህብረተሰቡ ሃሣቡን በነፃነት የመግለጽ መብትን ማበረታታት፣
ማህበረሰቡ ለመረጃ ቅርበት እንዲኖረው ምቹ ሁኔታን በመፍጠር ወቅታዊና ትክክለኛ መረጃዎችን እንዲያገኝ ማድረግ፤
በማህበረሰቡ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ እንቅስቃሴ ውስጥ አጋዥ ሚና መጫወትና በህብረተሰቡ ውስጥ ዴሞክራሲያዊ ባህል እንዲጎለብት ማበረታታት፣
የማህበረሰቡ ታሪክ፣ ባህልና ቋንቋ የሚያጎለብቱና በሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጭ የሚያስተዋውቅ ተግባራትን ማከናወን፤
ለዞኑ ማህበረሰብ ጠቀሜታ ያላቸው ዜናና ፕሮግራሞችን ለህዝቡ ማሠራጨት፤
የመንግስት ስትራቴጂዎች፣ አቅጣጫዎች፣ ፖሊሲዎችና ህጎች ለህዝብ በማስተዋወቅ ዞናዊ ክልላዊና ሀገራዊ አንድነትን ማጠናከር፤
የማህበረሰቡን ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ተሳትፎ የሚያጎለብቱ መረጃዎችን ተደራሽ ማድረግ፤
በማህበረሰቡ ዘንድ የተጀመረውን የልማት፣ የመልካም አስተዳደርና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ዕውን ለማድረግ በራስ ቋንቋ ተሳትፎ ማጎልበት፤ ቋንቋውንና ባህሉን ለማሳደግ የሚደረገውን ጥረት ማገዝ፣
ማህበረሰቡን በመረጃ በማበልፀግ ለልማት፣ ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታና ለመልካም አስተዳደር መጎልበት የሚጠበቅበትን ድርሻ እንዲወጣ ማገዝ፣
የመንግስት ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎችን በህብረተሰቡ ዘንድ በማስረጽ ለብሔራዊ መግባባት መረጋገጥ እገዛ ማድረግ፣
ነፃና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መልኩ ማህበረሰቡ በህገ-መንግስቱ የተቀመጠለትን መብት ተጠቅሞ በሚዲያው ሃሣቡን እንዲገልጽ ማስቻል፣
የማህበረሰቡን ታሪክ፣ ቋንቋ፤ ባህላዊ እሴቶችንና ተፈጥሮአዊ እንዲሁም ሰው-ሰራሽ ገጽታዎች ማስተዋወቅ፣
ነፃ፣ ሚዛናዊና ፍትሃዊ መረጃዎችን ለማህበረሰቡ ማቅረብ፣
የዞኑ ማህበረሰብ የሚያከናውናቸውን አርአያነት ያላቸውን ተግባራት ማበረታታት፣
ማህበረሰቡ እርስ በእርስ እና ከሌሎች አጎራባች ማህበረሰቦች ጋር ተሞክሮዎችን እንዲለዋወጥ ምቹ ሁኔታ መፍጠር፣