| የቢዝነስ ዜናዎች


 • የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ከወንጀል ተግባር ጋር ግንኙነት ያላቸውን ከ600 በላይ የባንክ ሂሳቦች ማገዱን አስታወቀ። አገልግሎቱ ለኢዜአ በላከው መግለጫ ከወንጀል ተግባር ጋር ግንኙነት ያላቸው የባንክ ሂሳቦችን እንዳገደ አስታውቋል። ከህገ-ወጥ የውጭ አገራት ገንዘብ ማስተላፍ ወንጀሎች ጋር ግንኙነት እንዳላቸው የተጠረጠሩ 665 የባንክ ሂሳቦች እንዳይንቀሳቀሱ ማገዱን ነው የገለጸው። በአገልግሎቱ የታገዱት የባንክ ሂሳቦቹ ህጋዊ የውጭ አገራት ገንዘብ ማስተላለፍ ፈቃድ ሳይኖራቸው በህገ-ወጥ መንገድ በአገር ውስጥ እና በውጭ አገራት ከሉ አካላት ጋር ትስስር በመፍጠር በህገ-ወጥ መንገድ የገንዘብ ማስተላለፍ ተግባር ላይ ተሰማርተው የተገኙ መሆናቸው ታውቋል። በወንጀል ድርጊቶቹ ላይ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ተሳትፎ የነበራቸውን አካላት በህግ ተጠያቂ የማድረግ የተጠናከረ ሥራ በመከናወን ላይ ይገኛል ብሏል። የተለያዩ የወንጀል ድርጊቶችን በመፈፀም የተገኘን ሃብት ከህጋዊ ምንጭና በህጋዊ መንገድ የተገኘ በማስመሰል የመጠቀም ወንጀሎች አፈፃፀም በየጊዜው እየተቀያየረ ያለ ወንጀል ከመሆኑም ባሻገር ከወንጀል ድርጊቶቹ የተገኘው ሃብት ሽብርተኝነትን በገንዘብ በመርዳት ወንጀል መፈፀሚያ ጭምር የሚውል በመሆኑ የመከላከልና መቆጣጠር ስራው በተጠናከረ አግባብ በመከናወን ላይ ይገኛል። ስለሆነም የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎቱ ከባላድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት እነዚህን ወንጀሎች ለመከላከልና ለመቆጣጠር በሚያደርገው ሂደት ህብረተሰቡ መረጃና ጥቆማ በመስጠት የተለመደ ትብብሩን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርቧል።

  October 10, 2022

  | ቢዝነስ

 • ወደ ተለያዩ ሃገራት ከተላኩ የጨርቃ ጨርቅ እና አልባሳት ምርቶች 140 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ገቢ መገኘቱን የኢትዮጵያ ጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

  ኢንስቲትዩቱ የ2013 በጀት ዓመት የ11 ወር ዕቅድ አፈጸጸሙ ላይ በደብረ ብርሃን ከተማ በተወያየበት ወቅት ዋና ዳይሬክተሩ አቶ ስለሺ ለማ እንዳሉት፤ የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ዘርፉን ውጤታማነት ለማስፋፋት የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ተገንብተው ወደ ስራ ገብተዋል።
  በዘርፉ የተሰማሩ የውጭና የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ባለፉት 11 ወራት የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ የፈጠረውን ጫና ተቋቁመው ምርቶቻቸውን ለውጭ ገበያ አቅርበው 140 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር ገቢ መገኘቱን ተናግረዋል።
  የምርቱ መዳረሻዎች አሜሪካ፣ ካናዳ፣ ቱርክ፣ ጣልያን እና ጀርመን መሆናቸውን የጠቀሱት ዋና ዳይሬክተሩ÷ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት 90 በመቶ የነበረው የውጭ ገበያ አቅርቦት ወደ 60 በመቶ ዝቅ ማለቱን ጠቅሰዋል።
  የጨርቃ ጨርቅ ዘርፉን በማዘመንና ጥራትን በመጠበቅ በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ ለመሆን ዘንድሮ በመስኩ ምሁራን 22 ጥናትና ምርምሮች ተደርገው 11ዱ ተጠናቀው ለባለድርሻ አካላት እንዲደርሱ መደረጉን ጠቁመዋል።
  ዋና ዳይሬክተሩ እንዳብራሩት፤ በ2013/2014 የምርት ዘመን የዘርፉን የጥሬ እቃ አቅርቦት እጥረት ለማቃለል በ150 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ 170 ሺህ ቶን ጥሬ ጥጥ ለማምረት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

  August 16, 2021

  | ቢዝነስ

 • በዘንድሮው የልዩ ጣዕም ቡና የቅምሻ ውድድር ከ1 እስከ 5 ደረጃ የወጡ አሸናፊ ቡናዎች የቅምሻና የማስተዋወቅ ስነስርዓት ተካሂዷል።

  ዝግጅቱ የፕሬዚዴንሺያል አዋርድ አሸናፊ ቡናዎችን ለዓለም አቀፍ ገዥዎች ለማስተዋወቅ ያለመ መሆኑ ተገልጿል።
  የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ ወይዘሮ ጽዮን ተክሉ እንዲሁም የቡናና ሻይ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አዱኛ ደበላን ጨምሮ የቡና ማህበራት ኃላፊዎች፣ የኤምባሲ ተወካዮች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው ታዳሚዎች በዝግጅቱ ላይ ተገኝተዋል።
  በዘንድሮው የልዩ ጣዕም የቡና ውድድር እስከ 39ኛ ደረጃ ያገኙ ቡናዎች ዓለም አቀፍ ጨረታና ሽያጭ የፊታችን ረቡዕ እንደሚከናወን ኢቢሲ ዘግቧል።
  እስካሁንም ከተለያዩ ሀገራት 180 ዓለም አቀፍ ገዢዎች በጨረታው ለመሳተፍ ተመዝግበዋል ነው የተባለው።

  August 16, 2021

  | ቢዝነስ

 • በ2013 በጀት ዓመት ከ279 ቢሊየን ብር በላይ መሰብሰቡን የገቢዎች ሚኒስትር አቶ ላቀ አያሌው ገለጹ፡፡

  ሚኒስቴሩ 290 ቢሊየን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ የእቅዱን 96 ነጥብ 2 በመቶ ማሳከቱንም ተናግረዋል፡፡
  ሚኒስትሩ እቅድ አፈጻጸሙ ካለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ19 ነጥብ 6 በመቶ እድገት ወይም የ45 ቢሊየን ብር ብልጫ እንዳለው አስታውቀዋል፡፡
  የእቅድ አፈጻጸሙ የኮሮና ወረርሽኝ እና የትግራይ ክልል ሁኔታ እንዲሁም ሌሎች አካባቢዎች ላይ ያሉ ችግሮች ባሉበት የተገኘ በመሆኑ አበረታች ነው ማለታቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

  August 16, 2021

  | ቢዝነስ

 • በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከማዕድን ምርቶች 681 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ገቢ መገኘቱን የማዕድን እና ነዳጅ ሚኒስቴር አስታውቋል።

  ይህም ባለፋት ዓመታት ከተገኘው የውጭ ምንዛሪ ትልቁ በመሆን ተመዝግቧልም ነው የተባለው።
  በቀጣይ ዓመትም ከዘርፉ ከዚህ የተሻለ ለማግኘት እቅድ አስቀምጠን ወደ ተግባር ገብተናል ብሏል ሚኒስቴሩ።
  የማዕድን ሀብታችንም የኢኮኖሚው ዋልታ እንደሚሆን እየሄድንበት ያለው መንገድ አመላካች ነው ማለቱን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

  August 16, 2021

  | ቢዝነስ

 • በኢትዮጵያ የግሪክ አምባሳደር አና ፋሩ እና በኢትዮጵያ የሞሮኮ አምባሳደር

  ኑዝሃ ዓለዊ መሃመዲ ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ለሊሴ ነሜ ጋር ተወያዩ፡፡
  በውይይታቸውም አምባሳደሮቹ ስለ ኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት አማራጮች እና እድሎች ገለፃ የተደረገላቸው ሲሆን÷ በቀጣይ ሁለቱ ሀገራት ኢንቨስተሮቻቸውን ወደ ሀገራችን በመላክ የኢንቨስትመንት ፍሰቱን መጨመር ስለሚቻልባቸው መንገዶች መክረዋል፡፡
  በተጨማሪም÷ ኢንቨስትመንቱን በጋራ የማስተዋወቅ ስራ ላይ ተወያይተዋል፡፡
  ኮምሽነር ለሊሴ ነሜ የኮምሽኑን አዲስ የህንፃ ገፅታ ለአምባሳደሮቹ እንዳስጎበኟቸውም ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

  August 16, 2021

  | ቢዝነስ