| ጤና


 • የኢየሩሳሌም ከፍተኛ የህክምና ቡድን በኮንሶ ዞን ካራት ከተማ ነፃ የህክምና አገልገሎት ለመስጠት ካራት ከተማ ገቡ።

  የህክምና ቡድኑ ለተከታታይ አምስት ቀናት የሚቆዩ ሲሆን ከ10 ሺህ በላይ ህሙማንን ለማከም ዝግጁ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

  የጄዊሽ ቮይስ ኢንተርናሽናል የህክምና ቡድን ኮንሶ ማህበረሰብን በነፃ የህክምና አገልግሎት ለማገልገል ካራት ከተማ ሲደርሱ የኮንሶ ዞን ምክትል ዋና አስተዳዳሪ አቶ ገልገሎ ገልሾ፣ ካራት ከተማ ከንቲባ አቶ ፍሬዘር ኮርባይዶ እና ከፍተኛ የዞንና ከተማ አመራር እና የህክምና ባለሙያዎች ደማቅ አቀባበል አድርጎላቸዋል።

  ነፃ የህክምና አገልግሎት ለመስጠት ካራት ከተማ የገቡት እንግዶቹ ከ18 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት የመዲሃኒት፣ የህክምና ቁሳቁስ፣ የምርመራ ማሽኖች፣ የምርመራ ግብዓትና ሌሎች ቁሳቁስን አሟልተው መግባታቸው ታውቋል።

  ማንኛውም የጤና ችግር ምርመራና የማዳን ስራ ለማድረግና ህብረተሰቡን በነፃ ለማገልገል የገባው የህክምና ቡድን በካራት ከተማ በተደረገላቸው አቀባበል ተደስተው በሚኖራቸው ቆይታ ሁሉ አገልግሎቱን በብቃት ለመስጠት ዝግጁ መሆናቸውን በደስታ አስታውቀዋል።

  ነፃ የህክምና አገልግሎቱ ከነገ ህዳር 25 ጀምሮ ለተከታታይ አምስት ቀናት እንደሚሰጥ ይጠበቃል።

  መረጃው የኮንሶ ዞን መንግሥት ኮሚኒኬሽን ጉ/መምሪያ

  December 3, 2022

  | ጤና

 • በኢትዮጵያ ውስጥ የሚስተዋሉ የጤና ድንገተኛ አደጋዎችን መዘጋጀት፣ መከላከል፣ መለየት እና ምላሽ ለመስጠት የዘርፈ ብዙ የአደጋ ጊዜ ዝግጁነት እና ምላሽ ዋና ተግባር ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ይፋ ተደርጓል፡፡

  በመድረኩ የተገኙት የጤና ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰ እንደተናገሩት የኢትዮጵያ መንግስት በጤናው ዘርፍ በሁለተኛው ትራንስፎርሜሽን እቅድ ከተካተቱ ዋና ዋና ስትራቴጂካዊ አቅጣጫዎች ዉስጥ 'የማህበረሰብ ድንገተኛ የጤና አደጋ ዝግጁነትና ምላሽ አሰጣጥ ስርዓትን ማሻሻል'' የሚለው አንዱ መሆኑን ተናግረው ከጊዜ ወደ ጊዜ አሳሳቢነቱ እየጨመረ የመጣውን የህብረተሰብ ድንገተኛ ጤና አደጋዎችን ተጋለጭነትን ከመከላከልና ፈጣን ምላሽ ከመስጠት አኳያ ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ ዘርፈ ብዙ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡

  እንደ ዶ/ር ሊያ ገለጻ የህብረተሰብ ድንገተኛ ጤና አደጋዎችን መቋቋም እና ፈጣን ምላሽ መስጠት የሚያስችል የጤና ስርዓት ለመገንባት የማህበረሰቡን እና የተለያዩ ሴክተሮችን የዘርፈ ብዙ ቅንጅትን የሚጠይቅ በመሆኑ ሁሉም አካላት በትብብር መስራት እንደሚገባው ገልጸው ዛሬ ይፋ ያደረግነው ዋና ተግባር ድንገተኛ የጤና አደጋዎችን መቋቋም ላይ እየተሰሩ ያሉትን ተግበራት ይበልጥ ያጠናክራሉ ብለዋል፡፡

  የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መሳይ ሀይሉ በበኩላቸው ለድንገተኛ የጤና አደጋዎችን ስርዓትን ለማጠናከር ዝግጁነት፣ ቅኝት እና ምላሽ ላይ ያተኮሩ ምሰሶዎች ተግባራዊ በማድረግ እና የሚመለከታቸውን ሴክተሮች በማቀናጀት የህብረተሰብ ጤና አደጋዎች ከመነሳታቸው በፊት ቀድሞ በመዘጋጀት እና ፈጣን ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል በሰው ሀይልና በማቴሪያል የተደገፉ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል፤ የተዘጋጀው መድረክም ይህን ለማጠናከር የሚረዳ ነው ብለዋል።

  የአለም ጤና ድርጅት የኢትዮጵያ ተወካይ ዶ/ር ቡሬማ ሃማሳምቦ የዓለም ጤና ድርጅት የአፍሪካ ክልላዊ ጽህፈት ቤት (WHO AFRO) የአባል ሀገራትን የህብረተሰብ ጤና ድንገተኛ አደጋ ዝግጁነት፣ መለየት እና ምላሽ የመስጠት አቅምን ለማሻሻል እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

  ኢትዮጵያ ፕሮጀክቱ ከተጀመረባቸው ጥቂት ሀገራት መካከል አንዷ መሆኗን ዶ/ር ቡሬማ ጠቁመው ለውጤታማነቱም አስፈላጊውን እገዛ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል፡፡

  የተላላፊ በሽታዎች ቅኝትና ምላሽ ስርዓቱን ማጠናከር፣ ለጎረበቤት አገራት በድገተኛ አደጋ ጊዜ ፈጣን ምላሽ መስጠት የሚችል ባለሙያ ማብቃት፣ የማህረሰቡን ግንዛቤና ተሳትፎ መጨመር እንደዚሁም የጤና ተቋማት፣ የክልል ላብራቶሪ፣ የመረጃ ስርዓትን ማደራጀትና ማጠናከር ላይ በልዩ ትኩረት በመስራት የዜጎቻችን የድንገተኛ የጤና አደጋዎች ተጋላጭነትን በመቀነስ አምራች እና የበለጸገ ህብረተሰብ መፍጠር ላይ ርብርብ ይደረጋል ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ አስቻላው አባይነህ ናቸው፡፡

  በውይይት መድረኩ ላይ የተለያዩ የፌደራል ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ በኢትዮጵያ ያሉ የኤምባሲዎች አምባሳደሮች፣ የጤናው ዘርፍ አጋር ድርጅቶች፣ የጤና ሚኒስቴር ተጠሪ ተቋማት ኃላፊዎች የተገኙ ሲሆን የህብረተሰብ ድንገተኛ ጤና አደጋዎች ዝግጁነት እና ምላሽን በማስተባበር ውጤታማነቱን ለማረጋገጥ በቅንጅት መስራት እንዳለባቸው ከመድረኩ ተሳታፊዎችም በስፋት ተነስቷል፡፡

  ከሁሉም ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት የህብረተሰብ ድንገተኛ ጤና አደጋዎችን መቋቋም የሚችል እና ፈጣን ምላሽ መስጠት የሚያስችል ጠንካራ ስርዓት ለመገንባት የሁለት ዓመት ዝርዝር ዕቅድ በቀጣይ ቀናት እንደሚዘጋጅም ከመድረኩ መገለጹን ከኢትዮጵያ ጤና ሚኒስቴር የተገኘ መረጃ ያመላክታል።

  November 23, 2022

  | ጤና

 • የዓለም የጤና ድርጅት ሶስት የኢቮላ ቫይረስ የሙከራ ክትባቶች በቀጣይ ሳምንት ወደ ኡጋንዳ እንደሚገቡ አስታውቋል፡፡

  ወደ ኡጋንዳ ሊላክ ከታሰበው የኢቮላ ቫይረስ የሙከራ ክትባት ሁለቱ በዩናይትድ ኪንግደም የተመረቱ ሲሆን የተቀረው ደግሞ በአሜሪካ የተሰራ ነው፡፡

  የዓለም የጤና ድርጅት የድገተኛ የጤና እክል ዳይሬክተር ሚሼል ሪያን እንደ ኢቮላ ያሉ ወረርሽኞችን ያለክትባት መቆጣጠር አዳጋች ነው ሲሉ የሙከራ ክትባቱ ውጤታማ መሆን ወረርሽኙን ለመከላከል ጠቀሜታ የጎላ ነው ብለዋል፡፡

  በኡጋንዳ ከባለፈው መስከረም ወር ጀምሮ የኢቮላ ቫይረስ ወረርሽኝ የተቀሰቀሰ ሲሆን እስካሁን በቫይረሱ 55 ሰዎች ሞተዋል አፍሪካን ኒውስ እንደዘገበው፡፡

  November 17, 2022

  | ጤና

 • በኢትዮጵያ የቲቢ እና መድሀኒት የተላመደ ቲቢን ፈጣን ሞለኪውላር መመርመሪያ ተደራሽነትን ለማሻሻል ከ3 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር በላይ የሚገመቱና በአሜሪካ የዓለም ዓቀፍ ተራድኦ ድርጅት (USAID) የተገዙ የ126 የጂን ኤክስፐርት ማሽኖች ርክክብ ተካሄደ፡፡

  በርክክቡ ወቅት ንግግር ያደረጉት የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰ ቲቢን ለማስወገድ የ5 አመቱ የጤና ስትራቴጂክ ዕቅድ ግቦችን ማስቀመጡን አስታውሰው ከውጤት ለመድረስ የየዕለት ትጋትን ይጠይቃል ብለዋል፡፡

  በስትራቴጂክ ዕቅድ ዘመኑ መጨረሻ በኢትዮጵያ ውስጥ በሚገኙ ወደ 1000 በሚጠጉ ወረዳዎች ቢያንስ አንድ የጂን ኤክስፐርት ማሽን እንዲኖር እቅድ የተያዘ ሲሆን አሁን ላይ ርክክብ የተደረገውን 126 ማሽኖች ጨምሮ 502 የጂን ኤክስፕርት ማሽኖች በኢትዮጵያ ውስጥ እንደሚገኙ ዶክተር ሊያ ገልፃዋል፡፡

  አክለውም ካለፉት አስርት አመታት ወዲህ ከአሜሪካ ዓለም ዓቀፍ ተራድኦ ድርጅት (USAID) እና ከሌሎች አጋሮች በተደረገው ድጋፍ መድሀኒት የተላመደን የቲቢ በሽታ በመለየት ረገድ ያሉብንን ክፍተቶች ለመለየትና ውጤታማነቱን የማስቀጠል ልምድን አጠናክሮ መቀጠል ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

  የአሜሪካ ዓለም ዓቀፍ ተራድኦ ድርጅት (USAID) በቲቢ ላይ የሚሰጠው ድጋፍ የቲቢ ምርመራን በማስፋፋት ላይ ብቻ የተወሰነ አይደለም ያሉት ዶ/ር ሊያ በኤም ዲ አር-ቲቢ ሕክምና ውስጥ ያለው ብሔራዊ የልህቀት ማዕከል ለኤም ዲ አር ቲቢ ቀጠና ማስፋፊያ፣ የእንክብካቤ አገልግሎቶችን ዲጂታል ለማድረግ፣ ለላብራቶሪ ድጋፍ፣ ለሥልጠና ማዕከል ድጋፍ እና የቲቢ የጥሪ ማዕከልን የማቋቋም ሂደትን እንዳካተተ ገልፀዋል።

  በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ትሬሲ አን ጃኮብሰን በበኩላቸው በኢትዮጵያ የቲቢ በሽታ ያለውን ጫና እና ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ የባለ 10 ቀለም የጂን ኤክስፐርት ማሽኖች ድጋፍ ማድረጋችን ትልቅ ሚና ይጫወታል ያሉ ሲሆን ፈጣን የሞለኪውላር ቲቢ ምርመራ ለማድረግ ያለውን ሰፊ ተደራሽነት ክፍተት ለማጥበብም የጎላ አስተዋፅኦ ይኖረዋል ብለዋል፡፡

  ርክክቡ በተከናወነበት ወቅት በቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ውስጥ የሚገኘው የኤም ዲ አር ህክምና አገልግሎት መስጫ ማዕከል በክብር እንግዶቹ መገኘታቸውን ከጤና ሚኒስቴር የተገኘ መረጃ ያመላክታል፡፡

  November 5, 2022

  | ጤና

 • ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት ለማህበረሰቡ ለመስጠት የሁሉም ባለድርሻ አካለት ትብብር አስፈላጊ መሆን የጤና ሚንስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ ገለጹ፡፡

  6ኛው ብሔራዊ የጤና ጉባኤ «የተቀናጀ ሰውን ያማከለ የጤና አገልግሎት ለተሻለ የጤና ስርዓት ውጤት እና መተማመን! » በሚል መሪ ቃል ተካሂዷል፡፡
  በዚህም እንደ ሀገር የተሻለ የጤና ስርዓት እንዲኖር የህክምና ተቋማትን ከማስፋፋት ባለፈ በዘርፉ የሚሰማራውን የሰው ሀይል ማብቃት ላይ ሊሰራ እንደሚገባም ተጠቁሟል፡፡
  በጤና ሚኒስቴር የጤና አገልግሎት ጥራትና ደህንነት ማሻሻል ቡድን መሪ ዶ/ር ደሳለኝ በቀለ፣ የህክምና እና የመድኃኒት አቅርቦት፣ የመሠረተ ልማት ችግሮች፣ አስፈላጊ የጤና አገልግሎቶችን በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች ለህብረተሰቡ ማድረስ ለተሻለ የጤና ስርዓት አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
  የጤና አገልግሎት ያሻሽላሉ የተባሉ ተቋማት ከመገንባታቸው ባሻገር የእናቶችና የጨቅላ ህፃናት ሞት እየቀነሰ መምጣቱንም ጠቁመዋል፡፡
  የኢትዮጵያ የህክምና ማህበር ፕሬዝዳንት ዶ/ር ተግባር ይግዛው በበኩላቸው በጤናው ዘርፍ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ ያለው ተቋማቱን ማስፋፋት ላይ በመሆኑ ብቃት ያለው ባለሙያ ማፍራት ላይ እንዲሁም የህክምና ቁሳቁስ ማሟላት ላይ ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰራ ይገባል ብለዋል፡፡
  በውይይቱ በጤናው ዘርፍ የተሠማሩ ዓለም አቀፍ ተቋማት፣ የሙያ ማህበራት እና ባለሙያዎች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

  August 16, 2021

  | ጤና

 • የዓለም የጤና ድርጅት የፈረንጆቹን 2021 ዓ.ም ዓለም አቀፍ የጤና እና ክብካቤ ባለሙያዎች ዓመት ብሎ ባወጀው መሠረት፣ በኢትዮጵያም በዛሬው ዕለት በይፋ መጀመሩን ጤና ሚኒስቴር ገልጿል።

  ዓለም አቀፍ የጤና እና ክብካቤ ባለሙያዎች ዓመት “መከላከል፣ ማልማት፣ እና አብሮነት” (Protect. Invest. Together) በሚል መሪ ቃል የሚከበር መሆኑ ነው የተገለጸው። ይህም ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት እና የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ለዘርፉ የሚያደርጉትን ኢንቨስትመንት እንዲያሳድጉ፣ የጤና ባለሙያዎች ለኮቪድ-19 መከላከያ ክትባት ቅድሚያ እንዲሰጣቸው፣ ምቹ እና ራሳቸውን ከአደጋ ለመካለከል የሚያስችል የሥራ ቦታ እንዲፈጠር እንዲሁም ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ከጤና ባለሙያዎች ጎን እንዲቆም የተግባቦት ሥራዎች መስራት ላይ ያተኩራል ተብሏል። የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ ዛሬ በተካሄደው የማስጀመሪያ መድረክ ባደረጉት ንግግር የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ከተከሰተ ጊዜ ጀምሮ የጤና ባለሙያዎች የከፈሉትን ከፍተኛ መሥዋዕትነት እና ኅብረተሰቡን ለማገልገል ያሳዩትን ከፍተኛ ጥረት በማሰብ ተገቢውን ምስጋና እና ዕውቅና ለመስጠት 2021 ዓ.ም ዓለም አቀፍ የጤና እና ክብካቤ ባለሙያዎች ዓመት ሆኖ ተሰይሟል ብለዋል።
  በኢትዮጵያም የጤና ባለሙያዎች የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመቆጣጠር እና ምላሽ ለመስጠት በሚደረገው ጥረት ላይ ግንባር ቀደም የሆነ ሚና ሲጫወቱ መቆየታቸውን አስታውሰዋል።
  በዚህም ወቅት ለኮቪድ 19 በከፍተኛ ሁኔታ ተጋላጭ ከመሆናቸው አንጻር ተገቢው ራስን ከበሽታ የመከላከያ ቁሳቁስ በማቅረብ፣ በኮቪድ 19 ዙሪያ ሥልጠናዎችን በመስጠት፣ ለኮቪድ-19 መከላከያ ክትባት ቅድሚያ እንዲያገኙ በማድረግ እና ሌሎች ተመሳሳይ ሥራዎች ሲሰሩ ቆይቷል ብለዋል። ኅብረተሰቡም ከቫይረሱ ራሱን በመጠበቅ በባለሙያዎቹ ላይ ያለውን ጫና በመቀነስ ወረርሽኙን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የሚደረገውን ጥረት መደገፍ አለበት ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።
  በመድረኩ ላይ ዓለም አቀፍ የጤና እና ክብካቤ ባለሙያዎች ዓመትን በይፋ ከማስጀመር በተጨማሪ በአገራችን የሚስተዋለውን የጤናው ዘርፍ የሥራ አጥነት ችግር ለመቅረፍ የሚያስችል ውልም የጤና ሚኒስቴር እና የተለያዩ የጤና ሙያ ማኅበራት መፈራረማቸውን ከጤና ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

  August 16, 2021

  | ጤና

 • በቻይና መንግሥት በሚተዳደረው ሲኖፋርም ኩባንያ የተመረተው የኮቪድ-19 ክትባት ለአስቸኳይ ጊዜ ጥቅም ላይ እንዲውል የዓለም ጤና ድርጅት ይሁንታውን ሰጠ።

  ድርጅቱ አርብ ዕለት የሲኖፋርም ክትባትን “ደህንነት፣ ውጤታማነት እና ጥራት” ማረጋገጡን ገልጿል፡፡
  የክትባቱ ፈቃድ ማግኘት የጤና ሠራተኞችን እና ለአደጋ የተጋለጡ ዜጎችን ለመከላከል የሚያስፈልገውን የኮቪድ-19 ክትባት ተደራሽነት የማፋጠን አቅም እንዳለውም ድርጅቱ አስታውቋል።
  ክትባቱ በአለም ጤና ድርጅት ይሁንታ ያገኘ ከምዕራባውያን ውጭ የተሠራ የመጀመሪያ ክትባት ሲሆን፣ ዕድሜያቸው 18 እና ከዚያ በላይ ለሆኑ ሰዎች በሁለት ዙር እንዲሰጥ ይመከራል፡፡
  የፋይዘር፣ የአስትራዜኔካ፣ የጆንሰን ኤንድ ጆንሰን እና ሞደርና ክትባቶች ቀደም ብለው ከዓለም የጤና ድርጅት ዕውቅና አግኝተዋል፡፡
  የተለያዩ ሀገራት ቀደም ሲል በተናጠል ለአስቸኳይ ጊዜ አገልግሎት እንዲውሉ የቻይናውያን ክትባቶችን መፍቀዱን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
  ሌላኛው ቻይና ሠራሽ ክትባት ሲኖቫክ በሚቀጥሉት ቀናት ውሳኔ ያገኛል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፣ የሩሲያ ስፑትኒክም በግምገማ ላይ ይገኛል ተብሏል፡፡

  August 16, 2021

  | ጤና

 • የአፍሪካ የበሽታ መቆጣጠሪያ እና መከላከያ ማዕከል ለአፍሪካ ሃገራት የሚሆን 220 ሚሊዮን የኮቪድ -19 ክትባት ማግኘቱ ተገለፀ፡፡

  በደቡብ አፍሪካ ከኤስፒኤን ጋር በተደረገው ስምምነት እ.አ.አ መስከረም 2022 ላይ 220 ሚሊዮን የጆንሰን ኤንድ ጆንሰን ክትባት ወደተለያዩ አፍሪካ አገራት እንደሚሰራጭ ተነግሯል፡፡
  በነሐሴ ወር የመጀመሪያው 6 ነጥብ 4 ሚሊዮን ዶዝ መድሃኒት ወደ 35 አገሮች ይላካሉ መባሉን ኢዜአ ኤስ ኤ ቢ ሲን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል።
  ይህ ክትባት የአፍሪካ ህብረት ልዩ መልዕክተኛ ስትራይቭ ማሲዪዋ የሚመራ ሲሆን በአፍሬክስም ባንክ የተገኘ ሁለት ቢሊዮን ዶላር ብድር ድጋፍ የተገኘ መሆኑ ተገልጿል፡፡
  የአፍሪካ አባል ሀገራት የኮቪድ -19 የማያቋርጥ የክትባት ስርጭት ለማካሄድ ስምምነት አጠናቃለች ተብሏል።
  የአፍሪካ ህብረት በኮቪድ-19 ልዩ መልዕክተኛ ስትራይቭ ማሲዪዋ ስለስምምነት ሲናገሩ ከደቡብ አፍሪካ የጆንሰን ኤንድ ጆንሰን ክትባቱ በዩኒሴፍ በኩል ወደ ተለያዩ አገራት እንደሚያጓጉዝ መረጃው አስታውሷል።

  August 16, 2021

  | ጤና